የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኤምባሲ-ዶሃ 

ርዕሰ ዜና

 

ወቅታዊ ጉዳይ

አዲሱ የኳታር የስራ ስምሪት በተመለከተ

 • አዲሱ የኳታር የሰራተኛና አሰሪ ህግ ከታህሳስ 21 ቀን 2009 ዓ/ም ( 30, Dec 2016 ) ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።

 • አዲሱን ህግን ጥሰው የሚገኙ ኩባንያዎች እርምጃ ይወሰድባቸዋል።

 • አዲሱ ህግ ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ለሆነው የውጭ ዜጋ የተሻለ ነፃነት የሚያጎናፅፍ ይሆናል።

በቅርቡ በኳታር የአስተዳደር ልማት፤ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኢሳ ቢን ሳኣድ አል ጃፋሊ አል ኑአሚ ከኳታር የዜግነት፣ ድንበርና የውጭ ዜጎች ጉዳዮች ረዳት ለጄነራል ዳይሬክቶሬት ብርጋዴር ሞሃመድ አህመድ አል አጢቅ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተመለከተው በሀገሪቱ የውጭ ዜጎች የስራ ስምሪትን ፍትሃዊና ቀልጣፋ በማድረግ የቀድሞውን የአሰሪ ወይም ስፖንሰር በሰራተኞች ከሃገር የመውጣትና መግባት እንዲሁም የስራ ስምሪት ዝውውርን የመቆጣጠር ስልጣንን የሚያነሳው አዲሱ የስራ ስምሪት አዋጅ እኤአ ከዲሴምበር 30 2017 ጀምሮ ስራ ላይ ውሏል።

በመግለጫው እንደተመለከተው ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከዚህ በኋላ በኳታር የሚገኙ ኩባንያዎች በአዲሱ አዋጅ ቁጥር 21/2015 የተቀመጠውን የውጭ ዜጎች ወደ ሃገር የመግቢያና መውጫ እንዲሁም የመኖሪያ ፈቃድ ህግን ተግባራዊ ስለማድረጋቸው ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የሚጀምር ይሆናል። በአሰራር ረገድም ህጉ የከፈላ ስርአትን በማስቀረት ከ2.1 በላይ ለሆነው በኳታር የስራ ስምሪት ውስጥ ላሉ የውጭ ሀገር ዜጎች የተሻለ ነፃነት የሚያጎናፅፍ፣ በስራ ውል ላይ በተመሰረተ አግባብ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችልና የተሻለ የስራ ዝውውር እንዲያደርጉ የሚያስችል ነውም ተብሏል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህጉን አፈፃፀም በየሳምንቱ በየወሩና አመታት እየገመገመ የሚሄድ ሲሆን ኩባንያዎችም ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ይሆናል።

ሚኒስትሩ አክለውም ሀገሪቱ በኳታር የመሰረት ልማት ግንባታ ንቁ ተሳታፊ የሆኑ ከ2 ሚሊዮን በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች አቅፋ መያዟ ትልቅ እድል መሆኑን ተናግረው አዲሱ ህግ የሰራተኞችን መብትና ጥቅማ ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ የመጀመሪያውን ትልቅ ደረጃ የተሻገረ ሲሉ ገልፀውታል። የቀድሞውን ከፋላ ስርዓት አስቀርቶ በዘመናዊና በስራ ስምምነት ውል የታጠረ የቅጥር ስነ−ስርዓት መኖሩ የሰራተኞችን መብት ከማስጠበቁም ባሻገር ከስራ ወደ ስራ የሚደረጉ ሽግግሮችን ቀላልና ቀልጣፋ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

ከወጡት ህጎች ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ማናቸውንም አይነት አስተያየቶችና ጥቆማዎችን እንደሚቀበሉ ያብራሩት ሚኒስትሩ ህጉ ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገው በስደተኛ ሰራተኞች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጣ በመታመኑ ነው ብለዋል።

 

 1. የውጭ ዜጎች ስራ መቀየር ሲፈልጉ እንዴት ይስተናገዳሉ?

 • በጊዜ ያልተገደበ (Open-Ended Contract) የስራ ስምምነት ውል የገቡ ሰራተኞችን በተመለከተ፤

 • በጊዜ ያልተገደበ የስራ ውል ያላቸው ሰራተኞች ያለ አሰሪው ፍቃድ ወደ ሌላ ስራ ለመዘዋወር አምስት ዓመት መጠበቅ አለባቸው።

 • በጊዜ የተገደበ (Fixed Contract) የስራ ውል የገቡ ሰራተኞችን በተመለከተ፤

 • የኮንትራት ጊዜያቸውን የጨረሱ የጊዜ ገደብ ኮንትራት ሰራተኞች ያለ አሰሪው ፍቃድ ወደ ሌላ ስራ መዘዋወር ይችላሉ።

 • የስራ ውል ጊዜያቸውን ያልጨረሱ ሰራተኞች ወደ ሌላ ስራ ለመቀየር የቀድሞው አሰሪያቸውን ፍቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል። ይህንን ፍቃድ ማግኘት ካልቻሉ የኮንትራት ጊዜያቸው እስኪያልቅ ድረስ ከቀጠር ውጭ መቆየት አለባቸው።

 • አንድ የውጭ ዜጋ ከኳታር የመውጫ ፍቃድ በህግ ቢከለከል ቤተሰቦቹም መውጣት አይችሉም ማለት ነው?        

 • አይደለም ቤተሰቦቹ መውጣት ይፈቀድላቸዋል።

 • አንድ የውጭ ዜጋ በኳታር የስራ ውል የጊዜ ገደቡን ጨርሶ ቢወጣ ለመመለስ ምን ያህል ጊዜ መጠበቅ ይኖርበታል?

 • አዲስ አሰሪ ካገኘ ወዲያውኑ መመለስ ይችላል።

 • አንድ የውጭ ዜጋ በኳታር የስራ ውል የጊዜ ገደቡን ሳይጨርስ ቢወጣ ለመመለስ ምን ያህል ጊዜ መጠበቅ ይኖርበታል

 • በጊዜ የተገደበ የስራ ውል (Fixed Contract) ጊዜውን ሳይጨርስ ከሀገር የወጣ ግለሰብ ተመልሶ ወደ ኳታር ለመግባት የስራ ውሉን ማለቅ (በውሉ መሰረት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ) መጠበቅ ይኖርበታል። ለምሳሌ እኤአ በ2018 የሚያልቅ የስራ ስምምነት ውል ፈርመው እኤአ በ2016 የስራ ውሉን አፍርሰው ከኳታር ቢወጡ ተመልሰው ለመግባት ሁለት ዓመት ያህል መጠበቅ የግድ ይሆናል ማለት ነው።

 • በሌላ በኩል በጊዜ ያልተገደበ የስራ ውል (Open-Ended Contract) ፈርመው አምስት ዓመት ሳይሞላቸው ከሀገር የሚወጡ ግለሰቦች በጊዜ ያልተገደበ ኮንትራት ውል መሰረት አምስት አመት መጨረስ ስላለባቸው። ተመልሰው ለመምጣት የአገልግሎት ጊዜያቸውን አስልተው አምስት ዓመት ለመሙላት የቀረውን ያህል ጊዜ መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

 • አንድ የውጭ ዜጋ ከሚሰራበት ኩባንያ ኮንትራቱን ሳይጨርስ ቢሰናበት ሌላ ስራ ለማግኘት ምን ያህል ጊዜ ይኖረዋል?

 • አንድ የውጭ ዜጋ ከሚሰራበት ኩባንያ ኮንትራቱን ሳይጨርስ ቢሰናበት ጉዳዩን ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች አስተዳደር ክፍል በማሳወቅ ሌላ ስራ ለማግኘት የ3 ወር ጊዜ ይኖረዋል። በተሰጠው የ3 ወር ጊዜ ውስጥ ሌላ ስራ ለማግኘት የቻለ ሰራተኛ አዲሱን የቅጥር ኮንትራት ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ማቅረብ ይጠበቅበታል። በተሰጡት 3 ወራት ውስጥ ሌላ ስራ ማግኘት ካልቻለ ግን ኳታርን ለቆ መውጣት ይኖርበታል።

 • አንድ ሰራተኛ ከኮንትራት ውሉ ጊዜ ቀድሞ ስራ መልቀቅ ቢፈልግ ህጉ እንዴት ያስተናግደዋል?

 • አንድ ሰራተኛ ከኮንትራት ውሉ ጊዜ ቀድሞ ስራ መልቀቅ ቢፈልግ መጀመሪያ ከአሰሪው ፍቃድ ማግኘት ይኖርበታል። በሌላ በኩል ግን ሰራተኛው በአሰሪው በደል የሚፈፀምበት ከሆነና ለመልቀቅም ምክንያቱ ይህ ከሆነ አሰሪው በእርሱ ላይ በደል እንደፈፀመ ለፍርድ ቤት  ማስረጃ ማቅረብ አለበት። ማስረጃው አሳማኝ ሆኖ ከተገኘ ህጉ ሰራተኛው ወደ ሌላ አሰሪ መሄድ እንዲችል ድጋፍ ያደርግለታል።

 • የአገልግሎት ጊዜ እንዴት ይሰላል?

 • በአዲሱ ህግ መሰረት ሀሉም አሰሪና ሰራተኞች አዲስ የኮንትራት ውል ይዋዋላሉ። የኮንትራት ውሉም ተፈፃሚነት የሚኖረው ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ ይሆናል። ይህ ማለት ግን የአገልግሎት ክፍያንና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን በተመለከተ ከኮንትራት መፈራረሙ በፊት የነበሩ ጊዜያት አይቆጠሩም ማለት አይደለም።

 • የደመወዝ ክፍያን በተመለከተ፤

 • በአዲሱ ህግ መሰረት ማንኛውም ሰራተኛ ደሞዙን በኤቲኤም ወይም በባንክ አሰራር ክፍያው የሚፈፀም ይሆናል።

 • በዲሲፕሊን ችግር ከስራ የተወገዱ ሰራተኞች ቅጣት

 • በዲሲፕሊን ችግር ከስራ የተወገደ ማንኛውም ሰራተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ ይግባኝ እስካላቀረበ እና ጉዳዩ በይግባኝ ወደ ፍርድ ቤት ቀርቦም ይግባኙ ውድቅ የተደረገበት ከሆነ ተመልሶ ወደ ኳታር ለመግባት 4 ዓመታትን መጠበቅ ይኖርበታል።

 • የስራ ሰዓታት

 • መደበኛ የስራ ሰዓታት በሳምንት 48 ሰዓታት ብቻ ይሆናሉ ይህም የረመዳን ወርን አይጨምርም። በዚህ ወቅት የስራ ሰዓታት በሳምንት 36 ሰዓታት ብቻ ይሆናሉ።

 • የቤት ሰራተኞችን በተመለከተ

 • አዲሱ ህግ የቤት ውስጥ ሰራተኞችንም ይጨምራል።

 •  

 • ይመዝገቡ! ወደ ኳታር በገቡበት አጋጣሚ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው ሊያከናውኗቸው ከሚገቡ ስራዎች አንዱና ዋነኛው በኮሚኒቲ ማህበራችንና ኤምባሲያችን ቀርበው መመዝገብ መሆኑን አይዘንጉ!! ምዝገባው በየትኛውም ሰዓትና ሁኔታ ላይ ለሚያጋጥምዎ ችግር አፋጣኝ እርዳታ ማግኘት እንዲችሉ ሚሲዮኑም ዜጎቻችን የሚገጥማቸውን ችግሮች በመቅረፍ ሂደት ወሳኝ ምዕራፍ ይሄው የዜጎች ወቅታዊና የተሟላ መረጃ ይዞ መገኘቱ መሆኑን ማስታወስ እንወዳለን።  

ገጽ 2 

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ዶሃ

 News