የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኤምባሲ-ዶሃ 

 

ወቅታዊ ጉዳይ

ኳታር እንደ አገራችን ሁሉ በአለማችን ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ላይ ከሚገኙ ሃገራት ተርታ የምትሰለፍ ሃገር ስትሆን በተለይም እንደ አውሮፓውያኑ የጊዜ ቀመር እስከ 2030 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለማሳካት በያዘችው እጅግ ግዙፍ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት የማምጣት ትልሟን ለማሳካት የያዘችው እቅድ ተከትሎ በርካታ የስራ እድሎች የተመቻቹባትና በመላው አለም የሚገኙ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች የተሻለ ገቢ ለማግኘት መዳረሻቸው የሆነች ሃገር ናት።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ወደ ሃገሪቱ ለስራ የሚገቡ የውጭ ሃገር ዜጎች መብት፣ የስራ ላይ ደህንነትና  ሌሎች ጥቅማጥቅሞቻቸው ተጠብቀው መንቀሳቀስ እንዲችሉ አለማቀፉንና ክፍለ አህጉራዊውን የሰብዓዊ መብቶች የተመለከቶ ድንጋጌዎችን በማካተት የሰራተኞች አዋጅ ያወጣች ሲሆን ይህም በሰራተኛውና በአሰሪው መካከል ሊኖር ስለሚገባ ግንኙነት እንዲሁም ማንኛውም የውጭ ሃገር ዜጋ በሃገሪቱ ውስጥ በሚኖረው ቆይታ ወቅት ሊከተላቸው ስለሚገቡ የአኗኗር ዘይቤዎችና  ስነ ምግባሮችን ያካተቱ የህግ ማዕቀፎችን አውጥታ ተግባራዊ አድርጋለች። እነዚህ ህጎች መንግስት ሃገሪቱን ለማዘመን ካለው እቅድና ሃገሪቱ በተለያዩ ወቅቶች ከታማችባቸው የውጭ ሃገር ዜጎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ስርዓቶች ለማሻሻል እንዲሁም በ2022 የምታካሄደውን የአለም እግር ኳስ ዋንጫን የተሳካ ለማድረግ ካላት ፅኑ ፍላጎቶች ጋር ለማጣጣምም ማሻሻያ እያደረገችባቸው ትገኛለች። የያዝነው የፈረንጆቹ አመት መጠናቀቂያ ላይ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የተሻሻለው የሰራተኞች አዋጅም በተለይ በሰራተኛውና በአሰሪ ኩባንያ ወይም ግለሰብ /Sponsor or Kafil∕ መካከል የነበረውን ግንኙነት ይበልጥ ጤናማ በማድረግ ዜጎች መብቶቻቸው እና ጥቅማጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ከዚህ የአንበሳውን ድርሻ የነበራቸውን አሰሪውን ፈላጭ ቆራች የመሆን ያህል እድል ይሰጠው የነበረውን አሰራር ያስቀራልም ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኳታር ያለውን የስራ እድል በመጠቀም ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ የህንድ የኔፓል የፓኪስታን የፊሊፒንስ የግብፅ የባንግላዴሽ ዜጎችና ኢትዮጵያን ጨምሮ 63 የአለማችን ሃገራት ዜጎች ኑሮአቸውን በሃገሪቱ ያደረጉ ሲሆን ከ80 ከመቶ በላይ የሚሸፍነው ይህ የውጭ ሃገር ዜጋ በኳታር የሚኖረውን ህዝብ ቁጥር ከሁለት ነጥብ ሶስት ሚለዮን በላይ እንዲሆን አስችሎታል።

በኳታር የሚኖረው የሃገራችን ህዝብ ምንም እንኳ ከሃያ ሁለት ሺህ እንደማይበልጥ ቢገመትም ዜጎቻችን ከሃገር ቤት አንስቶ ወደ ኳታር እስኪገቡ ድረስ እንዲሁም ከገቡም በኋላ ቢሆን በቀጠር ከሚገኘው ከኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የኮሚኒቲ ማህበሩ ጽህፈት ቤት ቀርበው ምዝገባ የማያከናውኑ በመሆናቸው ፣ከሃገር ቤት ወደ ኳታር የሚገቡባቸው መንገዶች በአብዛኛው ከህገ ወጥ የቪዛ ንግድና የሰዎች ዝውውር ጋር የተሳሰረ በመሆኑም በዚህ በኳታር የሚገኘው የሃገራችን ዜጋ የስራ ሁኔታ እና የአኗኗር ዘይቤ የሚታሰበውን ያህል ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ለውጥ እንዳይታይበት ብሎም አላስፈላጊ የህይወት ዋጋ የሚከፈልበት ሆኗል።

ይህንን ሁኔታ ለመቀየር አዲስ የውጭ ሀገራት ስምሪት አዋጅ ወጥቶ ተግባራዊ ለማድረግ እይተሰራ መሆኑ ይታወቃል። አዋጁ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲሆንም ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል፣ የዜጎችን መብትም የሚያስከብርና የባለድርሻ አካላትን ሀላፊነት በግልጽ የደነገገ እንደመሆኑ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ ተስፋ ተጥሎበታል። ይሁንና ዜጎች ከሃገር ቤት ውጭ የስራ ስምሪት በሚያደርጉበት ወቅት ለሚገኙበት ሃገርም ህጎች ተገዢ መሆን እንዳለባቸው የግድ እንደመሆኑ ወደ ኳታር በሚደረገው የስራ ስምሪት ወቅት ዜጎቻችን ልብ ሊሏቸው ይገባቸዋል የምንላቸውን ዋና ዋና የህግ ድንጋጌዎችና አከባቢያዊ ሁኔታዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

  1. ዜጎቻችን በማንኛውም መንገድ /በማህበራዊ ሚዲያ እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች፣ በሃገር ቤት፣ ከኳታር፣ከመካከለኛው ምስራቅ እና ሌሎች የውጭ ሃገር ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች እንዲሁም ከቅርብ የቤተሰብ አባላትና ወዳጆቻቸው / የሚያገኟቸውን አማራጮች በመጠቀም በውጭ ሃገር  የስራ ስምሪት ከማድረጋቸው በፊት ስለ ኤጀንሲውም ሆነ አሰሪ ግለሰብና ኩባንያ ህጋዊነት፣ የስራ ስምሪቱ የሚጠናቀቅበት ወቅት፣ የደመወዝ ሁኔታ፣ የስራ ሰዓታት እና እንደ መጠለያ፣ ምግብ፣ የአመት ዕረፍት፣ የአየር ቲኬት ከመሸፈንና የመኖሪያ ፈቃድ ማውጫና ማሳደሻ የመሳሰሉ ሌሎች ጥቅማጥቅሞች የሚጠበቁ ስለመሆናቸው እና የስራ ቦታውና እይነት በተመለከተ በግልጽ ማወቅና  መረዳት ይጠበቅባቸዋል። ይህ የሚሆነው ምንም አይነት የስራ ስምምነት ውል ከመፈጸሙ በፊት ሲሆን በተለይ ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲው የቀጣሪውን ወይም የአሰሪውን (ኩባንያውን በተለመከተ በባለቤትነት የሚያስተዳድረውን ኳታሪ በሃገሩ አጠራር ከፊል የሚባለውን)  ሙሉ መረጃዎች/ ስም አድራሻ ስልክና ፋክስ/ እንዲሁም ከኤርፖርት ተቀብሎ ወደ መጠለያ ወይም የስራ ቦታ ስለሚደርስበት ሁኔታ ዝርዝር መረጃዎችን መያዝና ከሃገር ቤት ከመውጣታችሁ አስቀድሞ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የስልክ ልውውጥ በማድረግ የመረጃዎቹን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ይጠበቅባችኋል።

  2. በሃገሪቱ ስላለው የስራ እድልና ተዛማጅ የኑሮ ሁኔታዎች በተመለከተም  ኳታር ነዋሪ ከሆነ ወይም ከዚህ ቀደም ይኖር ከነበረና በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ ካለው ግለሰብ እንዲሁም ሌሎች ምንጮች ማጣራት አስፈላጊነቱ  የግድ ነው። ይህም ማድረግ የሚጠበቅብን በሃገራችን ባለው ሁኔታ በርካታ የውጭ ሃገር ስምሪቶች የሚደረጉት በህገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት በመሆኑና አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎችም ቢሆን ከዜጋው ይልቅ ለራሳቸው ደህንነትና ጥቅም ብቻ የሚቆረቆሩ እንደመሆናቸው አሁን በተጨባጭ በዜጎቻችን ላይ እየደረሱ ያሉ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ብሎም እንግልትና ሞት ምንጫቸው እነዚሁ አካላት የሚከናውኗቸው አማላይ የማስታወቂያ ስራዎች በመሆናቸው ነው። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋችን የውጭ ሃገር የስራ ስምሪት ከማድረጉ አስቀድሞ ስለሚሄድበት ሃገር አጠቃላይ መረጃ ከታማኝ ምንጭች ማሰባሰብ ይጠበቅበታል።

  1. ወደ የትኛውም የአለማችን ክፍል በተለይም  ወደ ኳታር የስራ ስምሪት ጉዞ ከማድረጋችን በፊት ልንዘነጋው የማይገባን ሌላው ጉዳይ ቢኖር የስራ ስምምነት ውል፣የፓስፖርትና ሌሎች የጉዞ ሰነዶቻችን ፎቶ ኮፒ በቀላሉ ልንገናኘው ከምንችለው የቤተሰብ አባል ወይም ግለሰብ እጅ ማስቀረት ነው። የአሰሪው ድርጅት ወይም ግለሰብ ሙሉ አድራሻዎች እንዲሁም የስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲውን የተበለከቱ  ጥቅል መረጃዎችን ሃገር ቤት ለሚገኝ ይሄው የቤተሰባችን ወይም የቅርብ ሰው እጅ ኮፒ አድርጎ ማስቀመጥ ያሻል።

  2. ከትምህርትና ስልጠና እና ከቤተሰብ ጋር የተያያዙ ሰነዶች በአጠቃላይ ህጋዊነታቸውና ወቅታቸውን ጠብቀው የታደሱ ለመሆናቸው በሃገር ቤት ከሚገኙ አግባብነት ካላቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች በዋናነትም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተረጋገጡ ሆነው መያዝ ይኖርባቸዋል። የስራ ውል ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊትም እንዲሁም የስራ ውል ስምምነት ሰነዱ ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መቅረብ እንደ አስፈላጊነቱም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚሰጠውን ልዩ ስልጠና መከታተል ያስፈልጋል። በኳታር የስራ ቋንቋ አረብኛና እንግሊዝኛ እንደመሆኑ በዚህ ረገድ ዜጎቻችን የተለየ ችግር እንደማያጋጥማቸው እርግጠኛ መሆን እንዳለባቸው ማስገንዘብ እንፈልጋለን።

  3. በማስቀጠልም በኤጀንሲው አልያም አሰሪው ግለሰብ/ኩባንያ በኩል የቀረበው የስራ ቪዛ አግባብነት ያለውና በኳታር በህጋዊ መንገድ በመንቀሳቀስ ላይ ካለ/የንግድ ፈቃዱ ከታደሰና ተፈላጊውን የስራ መደብ ተገልጾ የተዘጋጀ/ኩባንያ የተላከ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የቪዛውን ሁኔታ ከኳታር የሃገር ውስጥ ሚኒስቴር ድረ ገጽ በመግባት  Ministry of Interior's website  or http://eservices.moi.gov.qa/eservices-portal/pages/services ማመሳከርና የመኖሪያ ፈቃድ እስኪያገኙ ድረስ ያለውን ሂደት መከታተል ይችላሉ።

  4. ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የተሰማሩ አከላት እጅግ በርካታ ዜጎቻችንን በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት ተገቢነት ካለው ተቋም የተሰጠና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስራ ቤታቸን የተረጋገጠ የሙያ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንዲሁም ልምድና ክህሎት ሳይኖራቸው ከህገ ወጥ የቪዛ ነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር ቪዛዉን እንደሚያስወጡላቸው የሚታወቅ ሲሆን በዚህም ሳቢያ ኳታር ከደረሱ በኋላ ለጉልበት ስራ ያውም ህገ ወጥ የስራ ስምሪት እንዲያደርጉ በማስገደድ ለከፍተኛ እንግልትና ሁለንተናዊ ቀውስ እየዳረጉ መሆናቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል።  

  5. የአየር ቲኬት ላይ ያሉ መረጃዎችም ማለትም መነሻና መድረሻ ቦታ እንዲሁም በጉዞ ወቅት ስለሚከለከሉ እና ማድረግ ስላለብን ጥንቃቄዎች በቂ ግንዛቤ ሊኖረን እንደሚገባ ግልጽ ነው። በዚህ ወቅት እጅግ ወሳኝ የሆኑ ጥንቃቄዎችን እንድናደርግ የሚመከርበትና ህገ ወጥ ደላሎችን ከሌሎች ህጋዊ የሰራተኛና አሰሪ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሚለዩበት ጉዳይ ደግሞ በዚህ የስራ ስምሪት ወቅት መንገደኛው ከሚያከናውናቸው ክፍያዎች ጋር የተያያዙ ናቸው። በአብዛኛው የጎዞ ቲኬትና ሌሎች ከቪዛና ተያያዥ ክፍያዎች በአሰሪው በኩል የሚሸፈኑ ሲሆን እጅግ የተጋነነ ማለትም አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ቀጠር ለመምጣት የሚከፈለው ከ20 እስከ 70 ሺህ የኢትዮጵያ ብር እና ከዚያ በላይ ክፍያ የሚጠየቅበት ሁኔታ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። 

  6. ወደ ኳታር እንደገቡም ስልክ ለመደወል በተፈቀዱ አከባቢዎች በመሆን ከዚህ ቀደም ሃገር ቤት ሳሉ የያዙትን የተቀባይ አድራሻ መጠቀም ይችላሉ። ይህ በሚሆንበት ወቅትም ሃገር ቤት ከተፈረመውና በኤጀንሲው ቀርቦ በሃገራችን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እውቅና ተሰጥቶት ከተፈረመ የስራ ስምምነት ውል ውጭ ምንም አይነት አዲስ የስራ ውል መፈረም አይጠበቅብዎትም። ከዚህ በኋላ በሃገሪቱ ውስጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በአብዛኛው በአሰሪው ኩባንያ ወይም ግለሰብ ይሁንታ ላይ የተመሰረተ ሲሆን እንደ ማንኛውም የውጭ ሃገር ዜጋ ሁሉ በሃገሪቱ የተከለከሉ እና ልዩ ፈቃድ የሚያስፈልጋቸው ድርጊቶችን መለየትና ማወቅ ያስፈልጋል። ሃገሪቱ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ያለባት እንዲሁም በሼሪዓ የእስልምና ህግ የምትመራ ሃገር እንደመሆኗ ጥብቅ ጥንቃቄ ማድረግን ይጠይቃል።

  7. በእረኝነት፣ በቤት ሰራተኛነት እና በጉልበት ሰራተኛነት ተሰማርተው ለመንቀሳቀስ ለሚፈልጉ የውጭ ሃገር ዜጎች ሃገሪቱ የተለየ የስራ ህግ የሌላት በመሆኑ በነዚህ የስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ዜጎች ከፍተኛ በደል የሚደርስባቸው መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት በነዚህ የስራ ዘርፎች ላይ መሰማራትና ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመምጣት የሚሹ ዞጎች ላይ እገዳ መጣሉ ይታወሳል። በመሆኑም ህገ ወጥ ደላሎችና ሌሎች በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የተሰማሩ አካላትን ማማለያዎችን ወደ ጎን በመተው ለጊዜው በሁለቱም ሃገራት መንግስታት በተፈቀዱ የቤተሰብ እና የፕሮፌሽናል ሙያ ዘርፍ ከሚሰጡ/Skilled Labor, Professional Visa/ ቪዛዎች ውጭ ለጊዜው ምንም አይነት የጉልበት  እና የቤት ሰራተኝነት ቪዛዎች በኳታር ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናልብ።

  8. በኳታር የመኖሪያ ፈቃድና መጠለያ እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ሁኔታዎች ከተሟሉ በኋላም ሃገር ቤት ላይ የተፈረመው የስራ ስምምነት ውል ተቀባይነት ስለማግኘቱና ስምምነቱም የስራ አይነትና ድርሻ፣ ደመወዝ የስራ ሰዓት ኣና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች በአግባቡ ማካተቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

ገጽ 1 

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ዶሃ

 News